News

የምግብና የመድሃኒት ደህንትና ጤንነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን መ/ቤት ለምግብና ለመድሃኒት ደህንትና ጤንነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሠራ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በባለሥልጣን መ/ቤቱ የምግብ ደህንነት እና ጥራት ቁጥጥር አፈፃፀም በተመለከተ ያከናወነውን የክዋኔ ኦዲት ሚያዚያ 9፣ 2011 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ በካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በኦዲት ግኝቱ በተመለከተው መሠረት ባለሥልጣን መ/ቤቱ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አሰጣጥ የአሠራር ሥርዓት ባለመዘርገቱ ምክንያት የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሳይከናወን ከ2008-2010 ዓ.ም ለ37 የምግብ አምራች ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን፤ ከክልልም ሆነ ከባለሥልጣን መ/ቤቱ የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው ምግብ የሚያመርቱ፣ የጥራት መቆጣጠር ላብራቶሪ ሥራዎች የሚሰሩ ድርጅቶች መኖራቸውን እና መስፈርት ባለማሟላታቸው ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ እና የመድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ የተከለከሉ የምግብ አምራች ድርጅቶች ከባለሥልጣን መ/ቤቱ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ በመቆጣጠሪያ ኬላዎች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ከሚደረግ ምርምራ ውጪ ምግብ ሲከማች፣ ሲጓጓዝ፣ ሲከፋፈልና ለህብረተሰቡ ሲሰራጭ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ፍቃድ የማይሰጥ መሆኑ፤ ገበያ ላይ የዋሉ ምግቦችን ደህንነት እና ጥራት ለማረጋገጥ የድህረ ገበያ ቅኝት በማድረግ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ የማይወስድ መሆኑን፤ በአገር ውስጥ ለሚመረቱና ከውጭ ወደአገር ቤት በሚገቡ ማናቸውም የምግብ ዓይነቶች ላይ የምግብ ምዝገባ የማያከናውን መሆኑን በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
ማንኛውም የምግብ አምራች፣ ላኪ፣ አስመጪ ወይም አከፋፋይ ድርጅት ባለሥልጣን መ/ቤቱ ያወጣውን ወይም የተቀበለውን መስፈርት ተከትሎ ማንኛውንም ምግብ ጤናማ አጠባበቅ በማድረግ ቶሎ ቢበለሹ የሚችሉ ምግቦች በሚከማቹበት ለዕይታ በሚቀርብበት በሚታሸጉበት ወይም በሚጓጓዙበት ጊዜ ምግቡ በተገቢው የሙቀት መጠን መቀመጡንና መጓጓዙን ባለሥልጣን መ/ቤቱ ተገቢውን ክትትል የማያደርግ መሆኑ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡
ከምግብ ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ያላቸው ሰራተኞች የግል ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ በስራ ወቅት የምግብ ጥራት ደህንነት መጠበቂያ አልባሳት ሊጠቀሙ የሚገባ ቢሆንም በናሙና ከታዩ ሦስት የምግብ ማምረቻ ድርጅቶች ሁለቱ ድርጅቶች የምግብ ጥራት መጠበቂያ አልባሳት እንደማይጠቀሙና ያለጓንት በእጃቸው ወደ ማሸጊያ እንደሚያስገቡና በቂ የልብስ ማጠቢያ፣ የምግብ መመገቢያ ቦታ፣ የመፀዳጃ ቤት እና የገላ መታጠቢያ ቦታ ያልተሟላላቸው መሆኑ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ አስፈላጊ የሆኑትን የምግብ ጥራት ምርመራ ላብራቶሪዎች አደራጅቶ የተሟላ የምግብ ደህንነት ጥራት ቁጥጥር የማያደርግ መሆኑና ምርመራ የሚያደርገውም በዘይትና በጨው ምግቦች ላይ ብቻ መሆኑን እና በፌዴራልና በክልል አስተዳደሮች ያለውን አሠራር ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎች አለመሠራታቸው በኦዲቱ ተገልጾ ሰዎች የሚመገቧቸው ምግቦችና የሚጠቀሙባቸውን መድሃኒቶች ደህንነታቸውን በማረጋገጥ በሰው ልጅ ላይ የጤና ችግር ሳያስከትሉ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ብሎም ከኦዲት ግኝቱ አኳያ ተቋሙ እየሠራ ያለውን ሥራ እንዲያስረዳ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሔራን ገርባ በሰጡት ማብራሪያ የኦዲት ግኝቱ በተቋሙ የነበሩ ችግሮችን በማሳየት የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጠቃሚ እንደነበር ገልፀው ተቋማቸው ምግብን፣ መድሃኒትን፣ የጤና ተቋማትን፣ የጤና ባለሙያዎችንና የጤና ነክ ጉዳዮችን የሚቆጣጠር ክፍተኛ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ቢሆንም በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ያልተደረጀና ድጋፍ ሳያገኝ የቆየ መ/ቤት እንደነበር በመግለፅ የሚጠበቅበትን ያህል ሳይሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙን ለማጠናከር እና በዘርፉ የሚታዩትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ የተቋሙ የማቋቋሚያ አዋጅ መሻሻሉን፤ በክልሎች ያለውን የቁጥጥር ሥራ ለማጠናከር 2500 ለሚሆኑ የክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት መቻላቸውንና በዚህም የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ40 ሺህ በላይ የምግብ ተቋማት ላይ የኦዲት ምርመራ ለማድረግ መቻሉን፤ 70 % በሚሆኑት የምግብ አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ የድህረ ፈቃድ ምርመራ ማከናወን መቻሉን፤ አድራሻቸው የማይታወቅና ከባለሥልጣን መ/ቤቱ እውቅና ውጪ ፈቃዳቸውን ለሌላ ሥራ ሲያውሉ በቆዩ 205 ተቋማት ላይ የፈቃድ ስረዛና ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን፤ ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት ባለመዘርጋቱና የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱ ትልቅ ችግር የነበረበት መሆኑን በመረዳት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የኤሌክትሮኒክስ የቁጥጥር ሥርዓት ለመድኀኒት ምዝገባ መጀመራቸውንና የምግብ አምራቾች ፈቃድ አሰጣጥንም በኤሌክትሮኒስ ሥርዓት ለማድረግ በሙከራ ላይ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሔራን የላብራቶሪ መሠረተ ልማት በአገር አቀፍ ደረጃ የዋናው ባለሥልጣን መ/ቤትን ጨምሮ 4 ብቻ መሆናቸውንና የዋና መ/ቤቱ ላብራቶሪም ገና በመደረጃት ሒደት ላይ መሆኑን፤ በ5 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ የምግብና የመድሃኒት ላብራቶሪዎችን እየተደራጀ እንደሚገኝ፤ አሁን ላይ ከዘይትና ከጨው ምግቦች በተጨማሪ ሌሎች ምግቦች ላይ የድህረ ፈቃድ ቁጥጥር እየተከናወነ እንደሚገኝ፤ ወደአገር ቤት የሚገቡ ምግቦች ላይ የሚደረገው የጥራት ቁጥጥርም ከ13 ወደ 23 ዓይነት ማሳደግ መቻሉን፤ ምግብ አምራች ድርጅቶች የራሳቸውን የውስጥ ጥራት ማረጋገጥ ሥርዓት እንዲዘረጉ እየተደረገ እንደሚገኝ፤ አላሰራ ያሉ ህጎችን በማሻሻል ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምግቦች ላይ የሚደረገው የምግብ ምዝገባ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ መሠራቱን፤ በክልሎች ከሥራ አድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ የምግብ ማምረት ፈቃድ የሚሰጣቸው አካለት ተገቢውን ጥራት ደረጃ ይዘው ከመስራት አኳያ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ በሚጠየቅበት ጊዜ የተፈጠረላቸውን የሥራ እድል ለማደናቀፍ ተደርጎ እየተወሰደ በተቋሙ የቁጥጥር ሥራ ላይ በተለያዩ የመንግስት አካልት ጭምር ግፊትና ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ፤ ከክልሎች ጋር ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሞከረ መሆኑንና በተለይም ምግብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ክፍተኛ ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠር፣ የቁጥጥር ሥርዓቶችን በማዘመንና የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የተቋሙ ኃላፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ምላሽ በየዓመቱ የድህረ ገበያ የቅኝት ሥራዎች እንደሚሠራ፤ በመንግስት ሥር ያሉ የጥራት ምርምርና ቁጥጥር ላብራቶሪዎችን ከማጠናከር ባሻገር የግል የጥራት ላብራቶሪ መቆጣጠሪያ ተቋማት ወደዘርፉ እንዲገቡ እየተበረታቱ እንደሚገኝ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ 112,000.00 በላይ የምግብ መቀነባበሪያ ተቋማት ቢኖሩም የቁጥጥር ሥርዓቱ የሚያከናውን አካላት ቁጥር መጠኑ ዝቅተኛ በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የህዝብን ጤና ሊያውኩ የሚችሉ የምግብ ዓይነቶች ላይ ቅድሚያ በመስጠት የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈቃድ ለተከለከሉ የምግብ አምራቾች ከፌዴራል መ/ቤቱ ፈቃድ ሊያገኙበት የቻሉበትን ሁኔታም ክልል ተሸጋሪ ምግቦች በፌዴራሉ ተቋም ይስተናገዳሉ በሚለው ህግ መሠረት የተፈፀመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከከሰራተኞች ሥነምግባር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ የተጠረጠሩ 6 ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን፣ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች በየደረጃው መወሰዳቸውንና የግንዛቤ ማስጨበጫ የስነ-ምግባር ሥልጠናዎች ለቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጭምር መሰጠቱን፤ ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅለው የሚሸጡ አካላትን ለመቆጣጠር ከክልል መንግስታት ጋር የመቀናጀትና ክልል ተሸጋሪ ምግቦች ቁጥጥርና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ወጥ አሠራር በሚኖርበት አግባብ እየተሠራ እንደሚገኝ የተቋሙ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በተቋሙ አመራሮች የተሰጡ ምላሾችንና ተሰርተዋል የተባሉ ሥራዎችን ካዳመጠ በኋላ ተጨማሪ ትኩረት ያሻቸዋል ባላቸው የህፃናት ምግብ፣ የደረቅ እንጀራ ዝግጅት፣ ሌሎች ባዕድ ነገር እየተቀላቀለባቸው ወደገበያ የሚቀርቡ ምግቦች፣ የመድሃኒት አቅርቦትና አወጋገድ፣ የንግድ ፈቃድና ደረጃ አሰጣጥ፣ ወደአገር ውስጥ ያለምዝገባ በሚገቡ ምግቦች፣ የህብረተሰብ የግንዘቤ ማሳደጊያ ሥራዎች፣ ከባለድርሻ አካለት ጋር ተቀናጅቶ መሥራትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ዙሪያ ተቋሙ ልዩ ትኩረት በመስጠትና የአሠራር ሥርዓት በማሻሻል መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ባለሥልጣን መ/ቤቱ ኦዲቱ በናሙና ካያቸው ጉዳዮች ሰፋ አድርጎ በማየት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሊሰራ እንደሚገባ፤ በተለያየ ቦታ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሚያመርቱ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ፍቃድ በሚሰጡና እውቅና ሳይሰጣቸው የጥራት ማረጋገጫ በሚሰጡ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባ፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች በተመለከተ የወጣው ህግ በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ስለምርቱ ምንነት በምርቱ ላይ ሊገልፅ ይገባል ቢልም በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን፤ ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ሊሠራ እንደሚገባ እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤትም የባለሥልጣን መ/ቤቱ ችግሮች ከመፍታት አኳያ ትኩረት በመስጠት ሊደግፈውና ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ሊፈታለት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡


የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃዱን የከለከለው መስፈርቱን አሟልተው ባለመቅረባቸው በመሆኑ ክልሉ የከለከለውን ፈቃድ የፌዴራል መ/ቤቱ የሰጠበት አግባብ በባለሥልጣን መ/ቤቱ በኩል የተሰጠው ምላሽ ስህተት በመሆኑ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ይህን ፈቃድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በሰጡ ሠራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ሊያሳውቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዋና ኦዲተር አክለውም በኬላዎች ላይ የሚገቡ ምርቶች የናሙና አፈታተሸን በተመለከተ በተቋሙ ኃላፊዎች በተለያየ መድረክ የተለያዩ ተዓማኒነት የሚያሳጡ ምላሾች መሰጠታቸውን በመግለፅ በናሙና አፈታተሸ ላይ ተቋሙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ ተቋሙ የቁጥጥር ስርዓቱን ይበልጥ በራሱ ላብራቶሪ የሚያደርገውን የፍተሻ ሥራ አጠናሮ ሊቀጥል እንደሚገባ እና የምግብ ጥራት ችግር በህብረተሰብ ጤና ላይና በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል ባለመሆኑ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ጭምር ልዩ ቦታ ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ በመጨረሻ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ሊሠራ እንደሚገባ፤ በኦዲት ግኝቱ በተመላከቱ ግኝቶች፣ በአዲስ አበባ ተከስቶ በነበረው የአተት በሽታና የታሸጉ ውሃዎች ከጥራት ደረጃ በታች ሆኖ መገኘት መሠረት በማድረግ ከህግ አሠራር ውጪ በሚንቀሳቀሱ አካለት ላይ ህጋዊ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ እና በምግብ ደህንነትና ጤንነት ዙሪያ ተገቢውን መረጃ ለህብረተሰቡ በመስጠት ጤናው እንዲጠበቅ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *