News

አላግባብ የከፈሉትን ገንዘብ በማያስመልሱ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክር ቤቱ አሳሰበ

ከህግ ውጪ በመከፈሉ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለመንግስት ተመላሽ ይደረጉ ያላቸውን ገንዘቦች እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ 2011 ዓ.ም ድረስ ተመላሽ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ2002-2009 በጀት አመት በተለያዩ ኦዲት ተደራጊ የፌዴራል መ/ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው ኦዲት አላግባብ ተፈጽመው ተገኝተዋል ያላቸው ልዩ ልዩ ክፍያዎች ለመንግስት ተመላሽ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ከየተቋማቱ አመራሮችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 16፣ 2011 ዓ.ም ውይይት አድርጓል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ ያዋቀረው ልዩ ኮሚቴ ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የኦዲት ችግር ከታየባቸው የተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በኦዲት ግኝቶች ዙሪያ ውይይቶችን ማድረጉንና በህግና በአሰራር የሚፈቱ ችግሮችን የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸው ስራዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ እስከ ጥር 30፣ 2011 ዓ.ም ድረስ ባለመጠናቀቃቸውና ጊዜ የሚፈልጉ ጉዳዮች በማጋጠማቸው ልዩ ኮሚቴው እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ ስራውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤው ምክር ቤቱ በመንግስት የተመደበው በጀት ለህዝብ ጥቅም መዋሉን የመከታተል እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖሩን የማረጋገጥ ሀላፊነት እንዳበት ገልጸው ለዚህም ከፌዴራል ዋና ኦዲተርና ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር በመስራት አላግባብ የተከፈሉ ገንዘቦች ወደ መንግስት እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም መመለስ ያለባቸውን የመንግስት ገንዘቦች በተመለከተ ጉዳዩን በጠቅላይ አቃቢ ህግ በኩል ወደ ህግ አቅርቦ ተጠያቂ ከማስደረግ አስቀድሞ የተቋማቱ አመራር ሁኔታውን ፈትሾ በተባለው ጊዜ ውስጥ ለማስተካከል የሚችልበትን እድል ለመፍጠርና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በኦዲት ግኝት መሰረት አላግባብ በመከፈላቸው ለመንግስት ተመላሽ ይደረጉ ስለተባሉት ዋና ዋና ክፍያዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በሰጡት ማብራሪያ ከእነዚህ ክፍያዎች ውስጥ ህግና ስርአትን በመጣስ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ ህግና ስርአት ሳይኖር አስገዳጅ በሆኑም ሆነ ባልሆኑ ምክንያቶች የተከፈሉ ክፍያዎች፣ መከፈል ከሚገባው በላይ አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ በውል መሰረት በወቅቱ ላልቀረበ እቃና ላልተፈጸመ አገልግሎት እንዲከፈል ያልተደረገ የጉዳት ካሳ ይገኙበትል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ ሳይሰበሰብ የቀረ ቅድመ ክፍያ፣ ከደሞዝና ገቢ ላይ መቀነስ የነበረበት የገቢ ግብር፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ፣ ላልተሰራ ስራ የተከፈለ ደመወዝና ክፍያ እንዲሁም ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ ያልተሰበሰቡ ሂሳቦች እንደሚገኙበት ክቡር ዋና አዲተሩ አስረድተዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ ከ2002-2009 ድረስ የበጀት አመቱ በተደረገ ኦዲት ይመለስ ስለተባለው ገንዘብ ሲገልጹ በ2002 በጀት አመት 54.3 ሚልየን ብር፣ በ2003 በጀት አመት 12.4 ሚልየን ብር፣ በ2004 በጀት አመት 188.6 ሚልየን ብር፣ በ2005 በጀት አመት 333 ሚልየን ብር፣ በ2006 በጀት አመት 180.7 ሚልየን ብር በ2007 656.5 ሚልየነ  ብር በ2008 በጀት አመት 397.8 ሚልየን ብር እና በ2009 በጀት አመት 278.1 ሚልየን ብር በድምሩ 2.1 ቢልየን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን የተመለሰው 50 ሚልየን ብር እንደማይሞላ ገልጸው ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ በገቢ ረገድም በገቢዎችና ጉምሩክ ከ2002-2009 በጀት አመት ድረስ መሰብሰብ የነበረበት 12.5 ቢልየን ብር እንዳለ ገልጸው እስከ 2010 ድረስ የተሰበሰበው 1 ቢልየን ብር እንደሆነ ክቡር አቶ ገመቹ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም  በተሰብሳቢ ገንዘቡ ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ አለመውሰድና ኦዲቱን መሰረት በማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በየወቅቱ ለሚመለከተው አካል አለማሳወቅ የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በመግለጽ ተቋማት ወደህጋዊ እርምጃ ሳይገባ በፊት ግኝቶቹ በማስተካከል ላይ ጥረት ማድረግና የወሰዱትን እርምጃ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ክቡር አቶ ገለታ ስዩም ወደ ህጋዊ እርምጃ ከመግባት አስቀድሞ ተቋማት አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው ተቋማቸው በፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2009 በጀት አመት ኦዲት ግኝት መሰረት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ወደህግ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፋናንሻል ኦዲት ግኝት የሚመለከታቸው 170 ተቋማት እና የክዋኔ ኦዲት ግኝት የሚመለከታቸው 20 ተቋማት በድምሩ 196 ተቋማት ላይ   የግኝቶች ብዛት 150 የሚጠጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ እንደ ግኝቶቹ ክብደት ቅደም ተከተል እንደወጣላቸውና በመጀመሪያ ዙር 15 የፌዴራል ተቋማትና 20 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በድምሩ 35 ተቋማት እንደተለዩ አስረድተዋል፡፡

ክቡር አቶ ገለታ ለምርመራው 7 ጭብጦች መመረጣቸውንና እነርሱም የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ወጪዎች፣ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ወጪ፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ ሂሳብ፣ በንብረት አስተዳደር ላይ ያሉ ችግሮች በተለይም የጠፉ ንብረቶች፣ ለግንባታ ተጨማሪ ውል ከ30 በመቶ በላይ የተከፈሉ ወጪዎች እና የግዢ መመሪያን ያልከተሉ ግዢዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በየተቋማቱ በአሁኑ ወቅት ያሉ አዲስ አመራሮች በተፈጸሙት ስህተቶች ውስጥ ያልተሳተፉ ሊሆኑ ቢችሉም  ሀብቱን የማስመለስ ሀላፊነት እንዳባቸው የገለጹት ክቡር አቶ ገለታ ወደ ጥፋት የገቡ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ካሉ ከክሱ በፊት ገንዘቡን እንዲመልሱ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ ተቋማቱ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ  ገንዘቡን እስኪመልሱ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስፈላጊ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁንና እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ገንዘቡነም ለማስመለስ ምንም አይነት እንቅስቃሴ በማያደርጉት ላይ ግን ክስ እንደሚመሰርት ክቡር አቶ ገለታ አስታውቀዋል፡፡

በኦዲት ተደራጊዎች በኩል ከየራሳቸው ተቋም ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በስራ ሂደት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ያጋጠሟቸውንና በኦዲት ግኝትነት የቀረቡባቸውን ጉዳዮች በማንሳት አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በሰጡት አስተያየት የኦዲት ግኝቱ ትክክል ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ክስ ከመውሰድ ይልቅ ግኝቶቹ በቀጣይ እንዳይከሰቱ የሚያደርጉ ህጎችና አሰራሮችን ከመፍጠር አኳያ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ መወያየት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ እርምጃ አወሳሰድ ከመገባቱ አስቀድሞ በተሰጠው የ2 ወር ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን በተጨባጭ ማስመለስ ስለመቻሉ እንዲሁም ከአስገዳጅና አስቸኳይ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በክፍያዎች አፈጻጸም ላይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በደንብ ማጤን ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳይ ከስራ ባህሪያቸው አኳያ በተለየ ሁኔታ መታየት አለበት ብለዋል፡፡ በተቋማት በኩልም የውስጥ ኦዲትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ረገድም የአሰራር ክፍተቶቹ በሚወገዱበት ሁኔታ ላይ ተቋማቱን ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጸረ ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽን በኩል በዋናነት ምክር ቤቱ የኦዲት ግኝትን መሰረት አድርጎ ተጠያቂነትን በማምጣት ላይ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡

ክቡር አፈ ጉባኤው በሰጡት ምላሽ ልዩ ኮሚቴው ከኦዲት ተደራጊዎች ጋር ባደረገው ውይይት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የአሰራር ስርአት የማበጀት ጉዳይ በዝርዝር ውይይት እንደተደረገበትና ከፍተኛ ትምህርትን በሚመለከት አዋጁ ተሻሽሎ ለምክር ቤት እንደቀረበ በተመሳሳይም የክፍያ ተመኖች ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደቀረበ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች የፌዴራል ተቋማት አሳማኝ ያልሆኑ የተለያዩ ክፍያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ አስቀድመው ጥረት የጀመሩ ተቋማት ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና ያልጀመሩ ተቋማትም የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅተው በኦዲት የተመለከቱ ያልተሰበሰቡ ገንዘቦችን እስከ ሚያዝያ አጋማሽ 2011 ዓ.ም ድረስ ለመሰብሰብ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሰስበው ይህን በማያደርጉት ላይም ምክር ቤቱ ጉዳዩን ወደህግ እንደሚመራው አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *