News

ተቋማቱ የእርምት እርምጃዎችን በማስቀጠል አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ አንደሚገባቸው ልዩ ኮሚቴው አሳሰበ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና በአሁኑ ወቅት የሰላም ሚኒስቴር በሚል የተቋቋመው የቀድሞው የአርብቶ አደርና ፌዴራል ጉዳዮች በተገኙባቸው የኦዲት ግኝቶች ላይ መውሰድ የጀመሯቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በማስቀጠል ህጋዊ አሠራሮችን የጣሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ አንደሚገባቸው አሳሰበ፡፡ ልዩ ኮሚቴው ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ተቋማቱ በኦዲት ግኝቶች ዙሪያ ባለፉት ስድስት ወራት በወሰዷቸው የእርምት እርምጃዎች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ኦዲት ተደራጊ ተቋማት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2009 በጀት ዓመት ባካሄደው ኦዲት መሰረት የኦዲት አስተያየት ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸው (Desclaimer of openion) ናቸው፡፡

በውይይቱ ላይ ተቋማቱ ከ2002 እስከ 2009 በጀት አመት ድረስ የተገኙባቸውን የኦዲት ግኝቶች ለማስተካከል የወሰዷቸው እርምጃዎችና ለግኝቶቹ መነሻ የነበሩ ምክንያቶች በኃላፊዎቻቸው ተገልጸዋል፡፡

እንደ ሀላፊዎቹ ገለጻ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል ከተደረገው ጥረት በተጨማሪ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ሂሳብ ሚስጢራዊነቱን በጠበቀ መልኩ ኦዲት የሚደረግበትን አሰራር ለመዘርጋት ህጉን ለማሻሻል መታቀዱ፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በኩል ደግሞ ኦዲት ሊደረግ በሚቻልበት አግባብ የማቋቋሚያ አዋጁን በቅርቡ ማሻሻሉንና በተጨማሪም በውስጥ ገቢ አጠቃቀም፣ በግዥና በንብረት አስተዳደር ዙርያ የተለያዩ መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በሰላም ሚኒስቴር በኩልም የፋይናንስ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደሩ ያለበት ሁኔታ መገምገሙና በሰላም ሚኒስቴር ስር ካሉ 8 ተጠሪ ተቋማት ጋር የኦዲት የጋራ ፎረም በመመስረት የኦዲት ግኝቶችን ለማረም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጻóል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት የተቋማቱ አዳዲስ አመራሮች የኦዲት ግኝቶችን በማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳቸው  በበጎ ጎን ጠቅሰው በተቋማቱ በኩል ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለበትና የሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግስት ፈሰስ ማድረግ እንደሚኖርበት ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡  ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲም ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በማጥናት የሀገር ደህንነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ ከግብር ከፋዩ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሚዛናዊ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በኩልም ግዥዎችን በህጋዊ መንገድ ማካሄድ እንዲሁም በቢልዮን የሚቆጠር ብር ከፍተኛ ተሰብሳቢ ሂሳብ የሚታይበትን ሌተር ኦፍ ክሬዲትን በአግባቡ መምራት ይገባል ብለዋል፡፡ በሰላምሚኒስቴር በኩል የማስተካከያ ስራዎች እንደተሰሩ ቢገለጽም የ2010 በጀት አመት የኦዲት ሪፖርት ግን የተባለው መሻሻል እንደሌለ አንደሚያሳይ ገልጸው የሰላም ሚስቴር የችግሩን ስረ መሰረት በመፍታት ላይ ማተኮር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የልዩ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት በተቋማቱ አመራር በኩል የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ የተሻለ ጥረት መኖሩና ከህግ ማዕቀፍ፣ ከአሰራርና ከአደረጃጀት ጋር የተያያዙ የችግሮች መንስኤዎችን ለማስተካከል በተለይ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል አዋጁን በማሻሻል የተሄደው ርቀትና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በኩል ተቋሙ በበለጠ

ኦዲት እንዲደረግ ለማስቻል ህጉን ለማሻሻል ያለው ተነሳሽነት ጥሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከአቅም በላይ የሆኑ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ለማስመለስ መጣሩ በበጎ  የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተሰራ ጉልህ ስራ አለመኖሩን የጠቀሱ ሲሆን ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት ኤጀንሲ በቀር ተቋማቱ የተሰሩ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በዝርዝርና በገንዘብ መጠን አስደግፈው ገላጭ ሪፖርት ባለማቅረባቸው ኮሚቴው አስተያየት ለመስጠት እንዳልቻለ  ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ አመራሩ ቀሪ ስራዎችን ለይቶ ራሱን የቻለ የጊዜ ሠሌዳ አስቀምጦና በልዩ ሁኔታ ቅድሚያ ሰጥቶ በፍጥነት መስራት እንዳለባቸው የልዩ ኮሚቴው አባላት አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በማጠቃለያቸው አዲስ የተቋማት አመራሮች በተቋማቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸው  መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ለማረም የተደረገው ጥረት ጥሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ ከተልዕኮ አኳያ የህግ ማዕቀፎቻቸውን መፈተሽ አለባቸው ያሉት አፈ ጉባኤው የተጀመሩ የማስተካከያ ስራዎችን በማስቀጠል አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በሰላም ሚኒስቴር  በኩልም ከተጠሪ ተቋማት የኦዲት የጋራ ፎረም እና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ጋር በጋራ በመስራት ለችግሮች መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል ሲሉ የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ አስገንዝበዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ተቋማት በቀሪ ስራዎችና ውጤቶች ላይ እስከ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ድረስ ሪፖርት እንዲልኩ አሳስበዋል፡፡

ልዩ  ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2009 በጀት ዓመት ባካሄደው ኦዲት  አስተያየት ለመስጠት ካልቻለባቸው ሌሎች 4 ተቋማት ጋር ጥር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት ማደረጉ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *