News

ለመንገድ ደህንነት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱ አገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጋት መሆኑ ተገለፀ

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በመንገድ ደህንነት ዙሪያ በተገቢው መጠን ባለመሥራቱ አገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጋት መሆኑ ተገለፀ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተዘጋጀውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖረት መሠረት በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው መጋቢት 25/2011 ዓ.ም ከባለሥልጣን መ/ቤቱ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ ስብሰባ አኳሂዳል፡፡

በቀረበው የኦዲት ግኝት መሠረት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አደገኛ ቦታዎች ላይ የመንገድ ዳር ምልክትና የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያዎች ያልተተከለባቸው መንገዶች መኖራቸውንና የተሰሩትም እየወደቁ መሆኑን፤ መንገድ ተሰርቶ ለትራፊክ ክፍት ከመሆኑ በፊት የትራፊክ መልክቶች በትክክል ማሟላታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እንደማይሰራ፤ መንገዶች የሚገኙበት የየአካባቢውን አስተዳደር የትራፊክ ምልክት በአግባቡ እንዲተከሉ ማድረግ ቢኖርባቸውም ምላሽ እንደማይሰጡ እና ማንኛውም አካል በተሽከርካሪ ወይም በእግረኞች መንገድ እንቅስቃሴዎችን በሚያውክ መልኩ ቁሳቁስ ወይም ሸቀጥ እንዳያስቀምጥ፣ እንዳይነግድ፣ እንዳያበላሽና እንዳይቆፈር ከቆፈረ በኋላም እንዲደፍን የወጣውን ደንብ ተፈፃሚነቱን እንደማይከታተሉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በአሻራ በተደገፈ የመንጃ ፈቃድ አሠጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ቢኖርበትም በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ አለማድረጉን፤ በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አለመሆኑን፤ በህገ-ወጥ መንገድ የገቡ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች አስፈላጊውን ማስረጃና ሠሌዳ ቁጥር እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመሥራት ኃላፊነት ቢኖርበትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 104,345.00 እና በኦሮሚያ 25,000.00 በጠቅላላው 134,345.00 ሞተር ሳይክሎች ተመዝግበው ሰሌዳ ሳይሰጣቸው በመንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውንና ሞተሮቹን የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችም መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከ2 እስከ 5 ሰዎችን እየጫኑ በሰው ህይወት ላይ አደጋ እያስከተሉ እንደሚገኙ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡
ተቋሙ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ከማረጋገጥ፣ አስከፊ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ሀብቶች ውድመት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ አለመሆኑ፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራ በተቀመጠው ጊዜ የሚያከናውኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑና ዓመታዊ ምርመራ የተደረገላቸው ተሽከርካሪዎች ትክክለኛነትም ብዙ ጥያቄዎች የሚያስነሱ መሆኑ እና በባለሥልጣን መ/ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነቱን አስመልክቶ የወጡ አዋጆች ደንቦችና መመሪያዎች በየጊዜው በመገምገም መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን በመለየት የማሻሻያ ሥራ ቢሠራም ፀድቆ ሥራ ላይ ባለመዋሉ በቆዩ ህጎች እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልፆ ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት በሚጠበቀው ልክ እንዳይወጣ ህግና መመሪያዎችን እንዳይተገበር ያደረጉትን ጉዳዮች የተቋሙ ኃላፊዎች እንዲያስረዱ ጠይቋል፡፡
አቶ አብዲሳ ያደታ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በኦዲት ግኝቱ የተመላከቱ ችግሮች ከማስተካከል አኳያ ተቋሙ የተለያዩ የእርምትና የማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ተናግረው በአገሪቱ ያሉ የፌዴራል መንገዶች ሰፊ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመንገድ ላይ ምልክቶች በተለያዩ አካላት የሚመዘበሩበት፣ በአሽከርካሪዎች የሚገጩበት፣ ከቦታቸው የሚነሱበት ሁኔታዎች መኖራቸውን፤ በአንዳንድ ቦታ የመንገድ ሥራዎች ተሠርተው ሲጠናቀቁ የመንገድ ላይ ምልክቶች በተገቢው ሁኔታ መኖራቸውን አረጋግጦ የመረከብ ክፍተት መኖሩን እና የአሽከርካሪዎች ብቃትና ስነ-ምግባር ችግር የተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት እንደዚሁም የመንገድ አቀማመጠጥ ሁኔታ ለትራፊክ አደጋ የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ገልፀው ችግሮቹን ለመቅረፍ የተለያዩ ግምገማዊ ጥናቶች በማድረግ ካሜራ በመጠቀም መረጃዎችን በመያዝ አቅም በፈቀደ መጠን ምልክቶችና የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች /Speed Breakers/ በመንገዶች ላይ እንዲቀመጡ መደረጉን ገልጸው ለትራፊክ አደጋው ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው ግን የአሽከርካሪዎች ብቃትና ስነ-ምግባር ችግር በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የእውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከመንገድ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም አቶ አብዲሳ መንገድ የእግረኞችና የተሸከርካሪዎች መሆኑን ገልጸው ሁልጊዜም በፊት ለፊት የውይይት መድረክ፣ በሚዲያ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ የትራፊክ አደጋ ቀንን በማክበር፣ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመሆን ህገወጥ ንግድ በመንገዶች ላይ እንዳይካሄዱ የማድረግ፣ ከአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት እና መንገድ ትራፊክ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ግንባታዎች ያለአግባብ መንገዱን እንዳይሻሙና እንዳያውኩ ሚዲያን በመጠቀም በተለይም የፌዴራል አስፋልት መንገዶች አጠቃቀም ሥርዓት እንዲሻሻል በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫና የቁጥጥር ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተሸከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተገናኘ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የቁጥጥርና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ተጠናክረው መሠራታቸውን፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የተሸከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማዕከላት በችግሮች ላይ የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስዱ የማድረግ፤ ለተሸከርካሪ ቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች የመፍጠር፤ ሀሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ይዘው በተገኙት ላይም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ፤ በየማዕከላቱ የመንጃ ፈቃድ አሠጣጥ ሥርዓት ስታንዳርዱን የተከተለ መሆንን የመከታተል፤ በተለይም በዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በኦንላይን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መንጃ ፈቃድ የሚሠጥበት ሥርዓት የመዘርጋት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስከሚደረግም የማስተማር፣ የማሠልጠን፣ የወጡ ስታንዳርዶችን የማስጠበቅ፣ ህጎችን የማሻሻልና የመቆጣጠር ብቃትን የማሳደግ ሥራዎችን እየተሰሩ እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ከሞተር ሳይክሎች ጋር በተያያዘም አቶ አብዲሳ ሲያስረዱ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተሸከርካሪዎቹ እያመጡ ያሉትን ችግሮች መሠረት በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት አገራዊ ጥናት መደረጉንና ጥናቱንም ተከትሎ ህግ የማውጣት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙና ሞተሮቹ በድንበር በኩል በህገወጥ መንገድ የሚገቡ መሆናቸው ጋር ተያይዞ ከሚመለከተው አካል ጋር ተቋናጅቶ መሥራት እንደሚጠይቅ፤ ከተሸከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ምርመራ ጋር በተያያዘ ማዕከላቱን የማወያየት የቁጥጥር ሥራዎችን የመሥራት፣ ሙያተኞችና የተሸከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማዕከላት ላይ ጠንከር ያሉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በመሥራት የሦስት ወር፣ የስድስት ወር የእግድ እና ፈቃድ የመንጠቅ ተግባርት ማከናወናቸውን እና መንገዶች በፍጥነት ስታንዳርድ መቆጣጠሪያ እንዲመሩ ከማድረግ አኳያም የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች በደረጃ መዳቢዎች ተዘጋጅቶ በተለይም በተደጋጋሚ አደጋ አድራሽ ተብለው በተለዩ ተሸከርካሪዎች ላይ ለመግጠም የዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የህግ ማሻሻያዎችን በተመለከት ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ሲሰጡ ከተቋሙ መቋቋሚያ አዋጅ ጀምሮ የተለያዩ መመሪያዎችንና ደንቦችን የማሻሻል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ተጠናቀው ወደሥራ ሳይገቡ የቆዩ መመሪያዎችንም ተግባራዊ እንዲሆኑ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በባለሥልጣን መ/ቤቱ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘላቂነት መፍትሔ ከመስጠት አኳያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በተማሪዎች የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የግንዛቤ ማሳደጊያ ይዘቶች እንዲካተቱ እየተሠራ እንደሚገኝና በወቅታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ደግሞ በትምህርት ቤቶች በፕላዝማ ቴሌቪዥን እና በክበባት ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች እንዲተላለፉ የማድረግ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር የማዘጋጀት እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆንም የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ወደህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚወርዱበት ጊዜ በመንገድ ትራፊክ ደህንነትና አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልክቶች በተጨማሪነት እንዲያስተላልፉ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ምኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ህይወት ሞሲሳ በሰጡት ማብራሪያ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተከናወነው የክዋኔ ኦዲት በዘርፉ የሉትን ችግሮች ከማሳየት አኳያ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረው በመንገድ ደህንነት አጠቃቀም ችግር የተነሳ ከአገሪቷ ኢኮኖሚም በዓመት ከጂዲፒ ከ 1% እስከ 3% የሚደርስ እያሳጣ መሆኑንና በማህበረሰቡም ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ በመገንዘብ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በተለይም በዋናነት የአሽከርካሪዎችና የተሸከርካሪዎች ብቃት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ፤ የመንገድ ምልክቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው ሊቀመጡና ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው፤ አሁንም ቀጣይነት ያላቸው የግንዘቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለህብረተሰቡ ተጠናክረው ሊሰጡ፤ የትራፊክ ምልክቶች በአገር ውስጥ የሚመረቱበትና አቅርቦቱ አስተማማኝ የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር፤ በህገወጥ ተግባር ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ ተጠያቂነትንን የማረጋገጥ ሥራ ሊጠናከር፤ ተቋማት በቅንጅት ባለመሥራተቸው የተነሳ እየተበላሹ ያሉ መንገዶች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ እና የመንገድ ሃብት እንክብካቤ ደካማ በመሆኑ የመንገድ አስተዳደር አሰራር እንዲሻሻልና በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ጥናት ተጠናቆ ወደ ትግበራ የሚገባበት ደረጃ ላይ መደረሱን ወ/ሮ ህይወት ገልፀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባለት በባለሥልጣን መ/ቤቱ ሃላፊዎች የተሰጠውን ምላሽና ማብራሪያ መሠረት በማድረግ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ባለሥልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርጎ አሠራሩን ለማሻሻልና በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሄደበት እርቀትና የወሰዷቸውን ጅምር ማስተካከያ እርምጃዎች አበረታች መሆኑን አንስተው አሁንም ባልተሰሩ ሥራዎች ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኮሚቴው አባላት ሊስተካከሉ ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች በተለይም በህገወጥ መንገድ ወደአገር ውስጥ እየገቡ ያሉ የሞተር ሳይክል ተሸከርካሪዎች በህብረተሰቡ ላይ የአካልና የሕይወት አደጋ እያደረሱ በመሆኑ ህጋዊ አሠራርን ተከትሎ አገልግሎት እንዲሠጡ ከማድረግ አኳያ መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቻው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የመንጃ ፈቃድ አሠጣጥ ሰፊ የህገወጥ ተግባር የሚካሄድበት በመሆኑ በፈቃድ ሰጪውም ሆነ ወሳጁ ላይ በልዩ ትኩረት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር በመፈተሽ በዘረፉ ያሉ ችግሮች መፍትሔ ሊያበጅላቸው እንደሚገባ አሳስበው በተለይም ተቋሙ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎችን ሰርቻለው ቢልም የመንገድ ደህንነት በአግባቡ ባለመመራቱ በሰዎች ህይወት፣ በንብረትና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰና ከዓመት ዓመትም የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ በመሆኑ ተቋሙ እራሱን በሚገባ በመፈተሽ ፈጣን የማሻሻያ እርምጃ ሊወስድ ይጋባል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ሃሳብ ባለሥልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ ያዘጋጀው የድርጊት መርሃግብር በጥሩ ሁኔታና ዘርዘር ብሎ የቀረበ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን በቀረበው መርሃ ግብር መሠረት ተፈፃሚነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባና በመንገድ ደህንነት ችግር ምክንያት አገሪቱ በዓመት የጂዲፒውን እስከ 3 ፐርሰንት እያጣችበት መሆኑን፤ ችግሩ ሰብዓዊ ቀውሱ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነና ባለፉት ሦስት ዓመታት (ከ2007 አስከ 2009 ዓ.ም ድርስ) ብቻ ወደ 2.7 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት መድረሱን ተናግረው ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የተሸከርካሪዎች ብቃት፣ የመንገዶች ሁኔታ፣ የመንገድ ተጠቃሚዎች ሥርዓት፣ የመንገድ ምልክቶች በተገቢው ሁኔታ አለመቀመጥ ተደምረው ጉዳት እንዲደርስ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውና ችግሩንም ለመቅረፍ የተሸከርካሪዎች ቴክኒክ ብቃትን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ለአብነትም በ2009 ዓ.ም በናሙና በ4,147.00 ተሸከርካሪዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ብቁ ሆነው የተገኙት 892 ተሸከርካሪዎች (22%) ብቻ እንደነበሩና የተቀሩት ከደረጃ በታች መሆናቸውን ክቡር ዋና ኦዲተር ገልፀዋል፡፡
የመንጃ ፈቃድ ሰጪ አካላት እና የማሰልጠኛ ተቋማት ሥልጠና የሚሰጡባቸው መኪኖች ዘመናዊ ያልሆኑና ጊዜያቸውን የጨረሱ አሮጌ ተሸከርካሪዎች በመሆናቸው የተሟላ እውቀት ለሰልጣኞች እንደማይሰጡ፤ የተግባር ፈተና መስጫ ጊዜ መጠን በተሟላ ሁኔታ ተጠብቀው እንደማይተገበሩ፤ ከመንገድ ደህንነት ጋር በተያያዘ ተቋሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ባለመስራቱ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ችግርና አደጋ እያደረሰ እና ኢኮኖሚውንም እየጎዳ እንደሆነ፤ በሌላ በኩል የፍጥነት ወሰን ህግ ከወጣ 40 ዓመታት ቢያስቆጥርም እስከአሁን ተግባራዊ አለመደረጉን፤ የደህንነት ቀበቶ እንደ ሹፌሩ ሁሉ ተሳፋሪም ቀበቶ እንዲያስር የሚያስገድደው ህግ ተግባራዊ አለመደረጉን፤ ወደ አገር ውስጥ አገልግሎት ጊዜያቸውን የጨርሱ ተሸከርካሪዎች እንዳይገቡ ማድረግ ትኩርት እንደሚያሻው፤ የእግረኛ የመንገድ አጠቃቀምም ሥርዓት የተከተለ እንዲሆን የሚሠሩ ሥራዎች የአንድ ወቅት ተግባር ሳይሆኑ ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ሥርዓት ሊበጅላቸው፤ የሀሰት መንጃ ፈቃድ ባላቸው አካላት ላይም ባለሥልጣን መ/ቤቱ ተከታትሎ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እና ምክርቤቱም በቅንጅት ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ በማይሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል ቀልጣፋና ውጤታማ ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋት በኦዲት ግኝቱ የተመላከቱ ክፍተቶች እንዲታረሙ ኃላፊነታቸውን በአፋጠኝ ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀው የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎችንም ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *